Thursday, 16 August 2018

የጽድቅ መንገድ

 
የሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም ከመምጣቱ አስቀድሞ እውነተኛ የጽድቅ መንገድ አልታወቀም ነበር፡፡ ነገር ግን ዛሬ ሰማጣዊ አባታችን እግዚአብሔር እውነተኛውን የጽድቅ መንገድ አሳየን፡፡ ይኽውም የጽድቅ መንገድ የተባለ አንድ ልጁ ጌታችን  ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ከሱ በቀር ሌላ ወደ ሰማያዊ አባታችን ወደ እግዚአብሔር የሚወስድ የለም፡፡ እርሱ ጌታችን  ኢየሱስ ክርስቶስ እኔ የእውነትና የሕይወት መንገድ ነኝ በኔ በኩል ካልሆነ በቀር አንድም ወደ አብ የሚመጣ የለም ብሎ ተናግሮዋል፡፡(ዮሐ 14÷6)
       ስለዚህ እኛ ሁላችን ይህንን የማያሳስት እውነተኛውን  የጽድቅ መንገድ ክርስቶስን ብቻ ይዘን ከሄድን ዘወትር እየናፈቅን አባታችን ሆይ እያልን ከምንጠራው ከሰማያዊ አባታችን ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ሰማያዊ ሀገራችን ወደ መንግስተ ሰማያት እንደርሳለን፤ ዳግም በስራችን እንጸድቃለን መንግስተ ሰማያት እንገባለን ብለን አንመካም፤ የምንጸድቅበት ሃይማኔታችን ክርስቶስ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ ጌታችን  ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ እናንት ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ወደኔ ኑ እኔም አሳርፋችኃለሁ ቀምበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ›› ብሏል (ማቴ 11÷58)፡፡ እንዲህም ማለቱ በእኔ ጽኑ ሲል ነው፡፡
     ደግሞ ቅዱስ ጳውሎስ ጽድቅ በሃይማኖት ብቻ እንዲገኝ ስራ በመስራት እንዳይገኝ በጻፋቸው መልእክቶች ሁሉ ያስተምረናል፡፡ ‹‹ ሰው ስራ ሳይሰራ በሃይማኖት ብቻ እንዲጸድቅ እንውቃለን ›› ብሏል፡፡ (ሮሜ 3÷28) ከዚህም ቀጥሎ በ4ኛው ምዕራፍ በ4ኛውና በ5ኛው ቁጥር የሚሰራ ሰው ዋጋው አይቆጠርለትም እንዲያው እንደሚገባው ሰራ ይባላል እንጂ፡፡ የማይሰራ ግን ኃጢአተኛውን በሚያጸድቅ በእግዚአብሔር ቢያምን ማመኑ ጽድቅ ሆኖ ይቆጠርለታል ብሏል፡፡ ደግሞ ይልቁንም በጣም የሚያስረዳ በኤፌሶን መልእክቱ ‹‹ አምነን በጸጋው ድነናልና እናንተም የዳናችሁ በእግዚአብሔር ቸርነት ነው እንጂ በስራችሁ አይደለም ማንም የሚመካ እንዳይኖር ›› ብሏል (ኤፌ 2÷8-9) ዳግም ወደ ገላትያ ሰዎች በጻፈው በ2ኛው ምዕራፍ በ21ው ቁጥር ‹‹ የእግዚአብሔርን ጸጋ አልክድም የኦሪትን ስራ በመስራት የሚጸድቅ ከሆነ እንኪያስ ክርስቶስ ለከንቱ የሞተ ነዋ ›› ብሎ ተናግሮአል፡፡ ይህም ሰው ሁሉ በስራው እንዳይጸድቅ በእግዚአብሔር ጸጋና በክርስቶስ ሞት እንዲጸድቅ ያስረዳል፡፡ ክርስቶስ መሞቱ ሰው በስራው መጽደቅ የማይችል ስለ ሆነ ነው፡፡

ምንጭ:- የኢት/ኣ/ተ/ቤ/ክ '' የቤተ ክርስቲያን ጸሎት ''  ከሚለው መጽሐፍ ከገጽ 93 የተገኘ።

Tuesday, 14 August 2018

ከፍተኛ በዓል



ዝማሬውን አንሡ ከበሮንም ስጡ፥ ደስ የሚያሰኘውን በገና ከመሰንቆ ጋር በመባቻ ቀን በከፍተኛው በዓላችን ቀን መለከትን ንፉ (መዝ 81፥2-3) 

በዓለማችን ብዙ ዓይነት በዓላት አሉ ደግሞም ይከበራሉ። ነገር ግን ሁሉም ታላላቅ ወይም ከፍተኛ በዓላት አይደሉም። በክርስቲያኖች ዘንድ እጅግ የላቀ በዓል አለ እርሱንም ሁልጊዜ በልባቸው ይዘውት ይዞራሉ። ይህም በዓል እግዚአብሔር  በልጁ በጌታ ኢየሱስ ደም የተነሳ የሁላችንንም በደልና ኋጢአት ይቅር ያለበት ነው።

መፅሐፍ ቅዱስ ሲናገር በክርስቶስ መስዋህትነት የእግዚአብሔር ማዳን የጀመረው ወይም የታቀደው በመለኮት ጉባኤ ከዓለም ፍጥረት በፊት ሲሆን  (ራእ 13፥8 እና 1ኛ ጴጥ 1፥18-21) በማስመለጥ  ተምሳሌነቱ የታየው የእስራኤል ህዝብ ዓለምን ከምትወክለው ከግብፅ ባርነት አስወጥቶ ወደ ተስፋይቱ ምድር ሲያስገባ ነው። በመጨረሻም ይህ ማዳን ህያው የሆነው/ የተገለጠው በቀራኒዬ መስቀል ላይ የዓለም ቤዛ ኢየሱስ ቅዱስ ደሙን ሲያፈስ ነው።

እስራኤላዊያን ለብዙ ዘመናት ከነበሩበት ባርነት እግዚአብሔር በራሱ የጊዜ ሰሌዳ ቀጥሮ የሚያወጣበት ቀን አመጣ።  ይህ ቀን ለግብፅ ቤት የሀዘን፤ ለእስራኤል ቤት የምህረት ቀን ነበር። እግዚአብሔር በአንድ ሌሊት ሁለት ስራ ሰራ። አንዱም ህዝቡን ከግብፅ አወጣ አንድም ደግሞ ግብፅን በመቅሰፍት መታ።
ለአንዱ ሞት 
ለአንዱ ነፃነት 
በአንዱ ሌሊት

ታዲያ በግብፅ የሚኖሩ እስራኤላውያን መቅሰፍቱ ባለፈ ጊዜ እንዳያገኛቸው እግዚአብሔር እንዲያደርጉት ያዘዛቸው አንድ ነገር ነበር። ነውር የሌለበትን የበግ ወይም የፍየል ጠቦት ወስደው እንዲያርዱ፤ ከደምም ወስደው በሚገቡበት ቤት መቃኑንና ጉበኑን እንዲቀቡት ነበር። ደሙ በጉበኑና በመቃኑ ያለ ሰው መቅሰፍቱ ያልፈው ነበር። ደሙ በመቃኑና በጉበኑ የሌለ የግብፅ ቤት ግን መቅሰፍቱ ያገኘው ነበር።

እግዚአብሔር ይህን ብቻ አይደለም ለእስራኤል ያደረገው  '' በዚያም ቀን እግዚአብሔር የእስራኤልን ልጆች ከሠራዊታቸው ጋር ከግብፅ ምድር አወጣ። ''  (ዘጸ 12፥51) መውጣታቸውን ተከትሎ ምርኮ ሊያደርግ ከኋላ የመጣውን  እግዚአብሔር ለእስራኤል የሰጠው መፍትሄ የፈርኣንን ሰራዊት ዋጣቸው።
ለአንዱ መንገድ
ለሌላው ሞገድ

ከዚህም የተነሳ ሙሴና የእስራኤል ህዝብ ለእግዚአብሔር እንዲህ ብለው ዘመሩ

'' በዚያም ጊዜ ሙሴና የእስራኤል ልጆች ይህንን መዝሙር ለእግዚአብሔር ዘመሩ፥ እንዲህም ብለው ተናገሩ። በክብር ከፍ ከፍ ብሎአልና ለእግዚአብሔር እዘምራለሁ፤ ፈረሱንና ፈረሰኛውን በባሕር ጣለ። ጕልበቴ ዝማሬዬም እግዚአብሔር ነው፥ መድኃኒቴም ሆነልኝ፤ ይህ አምላኬ ነው አመሰግነውማለሁ፥ የአባቴ አምላክ ነው ከፍ ከፍም አደርገዋለሁ። እግዚአብሔር ተዋጊ ነው፥ ስሙም እግዚአብሔር ነው። '' (ዘፀ 15፥1-3)

እስራኤል ይህን የዘመሩት እግዚአብሔር ያደረገላቸው ትልቅ ስራ ስለነበረ ነው። ይህንን ነብየ እግዚአብሔር ዳዊት በመግቢያ ባለው መዝሙር እንደምናነበው በከፍተኛ በዓላችን ለእግዚአብሔቅ ዘምሩ ከግብፅ ባርነት መውጣታችን ይህ ለእስራኤል ስርአቱ ነውና ብሏል። (መዝ 81፥5)። አዎ ለእስራኤል እንደ ፋሲካ ያለ ከፍተኛ በዓል የለም። ለእኛ ለክርስቲያንስ?

እግዚአብሔር ነውር የሌለበት በግና ፍየል ሰውተው በመቃንና ጉበን ላይ እንዲቀቡ ያዘዘው ደም ወደ ክርስቶስ ኢየሱስ ደም ያመለከተ ነበር። የእግዚአብሔር በግ የሆነው ክርስቶስ ለእኛ መስዋዕት ሆኖ ደሙን አፍስሶ ከነበርንበት ጨለማ ነፃ መውጣታችን ወደሚደነቅ ብርሃን መምጣታችንን ከሚናገሩ ምሳሌ ዋንኛው ነው ማለት ይቻላል። የኤፊሶን መልእክት ፀሐፊ ሐዋርያው ጳውሎስ እንደተናገረው በበደልና በኋጢአታችን ሙታን የነበርን እኛን ክርስቶስ ባፈሰሰው ደም እንዲሁ በፀጋው ሕይወት ሰጠን ስሙ ይባረክ።

ዛሬ እኛ ክርስቲያኖች የቤታችን መቃንና ጉበን ላይ የበግና የፍየል ደም አንቀባም። ይልቁን በልባችን መቃንና ጉበን ላይ የጌታ ኢየሱስን ደም እረጭተናል በመሆኑም ከደሙ ኋይል የተነሳ የእግዚአብሔር ቁጣ ልክ የእስራኤልን ቤት ደሙን እያየ እንዳለፈ ሁሉ የእኛም የዘላለም መቅሰፍት ከእኛ አልፏል።

ዓመት እየጠበቅነው የምናከብረው በዓል ሳይሆን በእያንዳንዱ ዛሬ በተሰጠን የቀን እድል ማዳኑን እያወራን ወደ ፊት የምንዘረጋበት የዘላለም በዓል። ይህ በዓል በፍፁም በሌላ የማይተካና የማይደበዝዝ ሳያቋርጥ እስከ ወዲያኛው እጅግ በልባችን የታተመ ከፍተኛ በዓላችን ነው። በዓል ስል ስርአት አይደለም መለኮታዊ ሙላት እንጂ። ዓለም የማይሰጠን በጌታ ብቻ የሆነ ፍፁም ሰላም፣ መውጣት የሌለበት ፍፁም እረፍት፣ ሀዘን የሌለበት ፍፁም ደስታ፣ ግብዝነት የማያውቀው ፍፁም ፍቅር እረ ስሙ ይባረክ። ማን ይሄን ይሰጣል???