Tuesday, 4 August 2020

ምስለ ፍቁር ወልዳ ከመፅሐፍ ቅዱስ አንፃር በትንሹ ሲገመገም



ብዙዎቻችን '' ምስል ፍቅር ወልዳ '' የሚለውን ስዕል ሉቃስ እንደሳለው ሲነገር እንሰማለን። እንደ ሃይማኖቱን ለሚወድና የቤተክርስቲያን አባቶችን ቃል ከመጽሐፍ ቅዱስ ቃል በላይ ለሚወስድ የሚረገረውንም ነገር ያለ ጥያቄ ለሚቀበል ማንኛውም ሰው፤ ማርያም ጌታ ኢየሱስን አቅፋ የሚያሳየው ስዕል ደስ ሊያሰኘው ይችላል። ነገር ግን እንደ ባለአእምሮና አስተዋይ ሁሉን በቃሉ እንደሚመረምር ሰው ግን ለምንና እንዴት ያሉ መሰል ጥያቄዎችን መጠየቅና እውነቱን ለማወቅ መጣር አስፈላጊም ተገቢም ነው። 

እኔ ከጌታ እናት ማርያም አንዱ የምማረው ነገር '' ይህ እንዴት ይሆናል '' የሚለውን ጥያቄ ነው። " ማርያምም መልአኩን። ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ይሆናል? አለችው። " (ሉቃ1፥34) እንኳን ሰው ይቅርና መላእክት እያናገረህ ጥያቄ ጠይቆ እውነቱን መረዳት ከእሷ እማራለው። አዎ ይህ መሰረታዊና ዛሬ ለቆምኩበት እውነት ጠይቆ መረዳትንና ቃሉን መመርመር ወሳኝነት አለው። ዝም ብሎ ስለተባለና በዛ በሚባልበት ስፍራ ረጅም እድሜ ከነገሩ ጋር አብሬ መኖሬ የተባለውን ነገር እውነተኛ አያሰኘውም። 

ድንግል ማርያም ልጇን ይዛ ተስላለች ብሎ ለሚያምን ሰው ቢያንስ መሰረታዊ ጥያቄዎችን መጠየቅና መረዳት አለበት ብዬ አስባለው። በመጀመሪያ ደረጃ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ተቀረፀ ምስልና ስዕል ምን ይላል? የእግዚአብሔር ሀሳብስ ምንድነው? ብሎ መጠየቅ እጅግ መሰረታዊ ነው በተለይ በአዲስ ኪዳን። የሚገርመው በዛ በአሮጌው ኪዳን እንኳ እግዚአብሔር ይህን ብሏል......

" እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ስሜ ይህ ነው፤ ክብሬን ለሌላ፥ ምስጋናዬንም ለተቀረጹ ምስሎች አልሰጥም። " (ትንቢተ ኢሳይያስ 42፥8) ልጁን ቤዛ ሊቀካህን አርጎ በሾመበት አዲስ ኪዳን ደግሞ "፤ እግዚአብሔር መንፈስ ነው፥ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል። " (የዮሐንስ ወንጌል 4፥24) ተብሎ ተፅፏል። 

ሲቀጥል ወንጌላዊው ሉቃስን ሰዓሊ አርጎ ማምጣት ስዕሉን መንፈሳዊ ያደርገዋል ወይ? ይህን የምጠይቀው የብዙዎች መከራከሪያ ሉቃስ ስለሳለው ተቀባይነት እንዳለው አድርገው ማመናቸው ነው። አበበም ሳለው ከበደ ስዕሉ ምን ለውጥ አለው? 

ቅዱሳት መፃህፍት በእግዚአብሔር መንፈስ ስለመፃፋቸው ማስረጃ ማቅረብ ይቻላል ስዕል ግን ፍፁም የለም ??? 

ሌላው ሉቃስ ስሎታል የሚባለው ስዕል ኢየሱስ ህፃን እያለ በእናቱ እቅፍ ውስጥ ሆኖ ነው። ለመሆኑ ሉቃስና ኢየሱስ መች ነው የተገናኙት? የተሳለውስ ህፃን ሆኖ ነው ወይስ ካደገ በኃል በምናብ ነው? በጣም ደግሞ የሚገርመው የስዕሉ የአሳሳል ዘይቤ ድንግል ማርያም በምድራዊ በረከት እጅግ የከበረችና የናጠጠች ሐብታምና የቤተመንግስት ንግስት አስመስሎ መሳሉና ኢየሱስን ደግሞ እንደ ፊልም ማሳመሪያ ውብና ቆንጆ አድርጎ መሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ከነገረን ጋር እጅግ የሚጣላና የማይስማማ ያደርገዋል። 

ድንግል ማርያም ጌታን እንዴት እንደወለደችውና በምን ያህል ዋጋ በመክፈል እንዳሳደገችው ለሚያውቅ ሰው በተዋበ አልባስ፣ የወርቅ ፈርጥ ያለበት የሐር ልብስና የወርቅ አክሊል ሲያይ መጠየቅ ያለበት ጉዳይ አለ። መጽሐፍ ቅዱስ ሲናገር መስዋዕት ሲያቀርብ ጠቦት ለማምጣት ገንዘብ ላልበቃው ሰው የሰጠው አማራጭ ርግብ አንዱ ነው (ዘሌ 5፥7)። ድንግል ማርያምን ስሏታል የተባለው ሉቃስ የፃፈው ወንጌል ላይ ግን ያቀረበችውን ስንመለከት ግጭት ይፈጥርብናል። 

"፤ እንደ ሙሴም ሕግ የመንጻታቸው ወራት በተፈጸመ ጊዜ፥ በጌታ ሕግ። የእናቱን ማኅፀን የሚከፍት ወንድ ሁሉ ለጌታ የተቀደሰ ይባላል ተብሎ እንደ ተጻፈ በጌታ ፊት ሊያቆሙት፥ በጌታም ሕግ። ሁለት ዋሊያ ወይም ሁለት የርግብ ጫጩቶች እንደ ተባለ፥ መሥዋዕት ሊያቀርቡ ወደ ኢየሩሳሌም ወሰዱት። " (የሉቃስ ወንጌል 2: 22-24)

ኢየሱስን ደግሞ ይወደድ ዘንድ ደምግባት እንዳልነበረው (ኢሳ 53) እና የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ (ፊልጵ 2፥7) ተብሎ እንጂ እንደ HOME ALONE ሆሊውድ ፊልም ቆንጅዬ ሲያዩት የሚያሳሳ ድንቡሽቡሽ ልጅ እንዳልሆነ መረዳት እንችላለን። ይህስ ጥያቄ መመለስ የለበትም? 

ይህ ጉዳይ ሲነሳ እጅግ የሚደንቀኝ ነገር ደግሞ ሳለው የተባለው ሉቃስ ራሱ በፃፈው በሐዋርያት ስራ ላይ የፃፈው ትዝ ሲለኝ ነው። በነገራችን ላይ መጽሐፍ ቅዱስ ሉቃስ ባለመድሂት እንጂ ሰዓሊ እንደሆነ ምንም አልተናገረም። " የተወደደው ባለ መድኃኒቱ ሉቃስ " (ወደ ቆላስይስ ሰዎች 4፥14)። ምን እንዳለ ታውቃላችሁ? 

" እንግዲህ የእግዚአብሔር ዘመዶች ከሆንን፥ አምላክ በሰው ብልሃትና አሳብ የተቀረጸውን ወርቅ ወይም ብር ወይም ድንጋይ እንዲመስል እናስብ ዘንድ አይገባንም። " (የሐዋርያት ሥራ 17፥29)

እንዲህ ያለ ወንጌላዊ ከተናገረው ቃል በተቃራኒ ጊዜውን በእርድና በበርበሬ ቀለም ያጠፋል ብላችሁ ታምናላችሁ? አይመሰለኝም እንደው ነገሩን ለጥጣችሁ አላሰባችሁበት እንጂ ማሰቡንስ አታስቡም ነበር። 

አንድ የቤተክርስቲያን አባት በንግስ ጊዜ ይህን ምስለ ፍቁር ወልዳ ስዕል የሰንበት ትምህርት ቤት ዘማርያን ይዘው ሲዘምሩ ያዩና ይህ ህፃን እስካሁን በእናቱ እቅፍ ውስጥ ነው እንዴ ያለው? መች ነው የሚወርደው? ብለው ጠየቁ ይባላል። እናንተስ መቼ ከእናቱ እቅፍ ወርዶ በሰውና በእግዚአብሔር ፊት በቁመትና በሞገስ ካደገ በኃላ ስለ በደልና ኃጢአት ራሱን አሳልፎ በመስቀል ላይ ሞቶ ደግሞም እኔኑን ስለማጽደቅ በሶስተኛው ቀን ከሙታን ተለይቶ በመነሳት ለዘላለም እኖርበት ዘንድ ስፍራ ሊያዘጋጅል ወደ አባቱ በመሄድ በማያልፍ የሕይወት ኃይል በግርማ ቀኝ አልተቀመጠምን?  ብላችሁ የማትጠይቁት? 

ማስተዋል ይብዛላችሁ ከተፃፈው እንዳናልፍ ጸጋው ይርዳን አሜን።

Monday, 3 August 2020

መሻርና መፈጸም



“እኔ ሕግንና ነቢያትን ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ፣  ልፈጽም እንጂ ለመሻር አልመጣሁም፣(ማቴ. 5፡17)። (ክፍል አንድ)

ለዚህ ጽሁፍ መነሻ የሆነኝ፦ ብዙ ወንድሞቻችን እና አንዳንድ የቤተ ክርስቲያናችን ሊቃውንትና መምህራን “እኔ ሕግንና ነቢያትን ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ፣ ልፈጽም እንጂ ለመሻር አልመጣሁም፣” (ማቴ. 5፡17)፣ የሚለውን ኀይለ ቃል የሚረዱበት መንገድ የብሉይ ኪዳኑ ሕግ (የሙሴ ሕግ) አሁንም እንደሚሠራና በሐዲስ ኪዳንም ልንጠብቀው እንደሚገባን፣ ትእዛዝም እንደ ሆነ፣ ካልፈጸምናቸው ደግሞ እንደምንኮነንና የገሃነመ እሳት ፍርድ እንደሚጠብቀን ቆጥረው ሲጽፉና በፌስ ቡክ ላይ ሲለጥፉ ስላየሁ ነው። ምናልባት ለጸሐፊዎቹም ሆነ ለአንባቢዎች ይጠቅማል ብዬ ስላሰብሁ ይህን ጽፌአለሁና በትዕግሥት አንብቡት።   

ብዙ የቤተ ክርስቲያናችን መምህራን የብሉይ ኪዳኑና የሐዲስ ኪዳኑ አገልግሎትና ትምህርት ሲምታታባቸውና ምእመናንንም ግራ ሲያጋቡ ይስተዋላል። ለዚህ ለተምታታና ግራ ለተጋባ ትምህርት ምክንያት የሆናቸው የዕውቀትና የትምህርት ማነስ አይመስለኝም። ችግሩ የመጣው ኢትዮጵያ የብሉይ ኪዳኑን ሕግና አዲስ ኪዳንንም ተቀብላለች ከሚል አስተሳሰብና በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ ለሚታዩ አንዳንድ አይሁዳዊ ባህልና መንፈሳዊ ለሚመስሉ ሰው ሠራሽ ልምምዶች ሽፋን ለመስጠት የታሰበ አካሄድ ይመስላል። ሕጉን ተቀብላለች ወይም አልተቀበለችም የሚለውን ጉዳይ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ አሁን ማንሣት አስፈላጊም ጠቃሚም ባለመሆኑ እንተወዋለን (1 ጢሞ. 1፡7)። 

በቅድሚያ በማቴዎስ 5፡17 ላይ የተጠቀሰውን ኃይለ ቃል ትርጉም በሚገባ ለመረዳት፣ የሕጉን (የኦሪትን) ምንነት፣ ለማን እንደ ተሰጠና የተሰጠበትን ዓላማ መረዳት አስፈላጊ ነው። 

1ኛ. ሕጉ የተሰጠው በሲና ተራራ ለእስራኤላውያን ብቻ ነው፣ ሕጉ ለነ አብርሐም ይስሐቅና ያዕቆብ፡ ወይም ለአሕዛብ አልተሰጠም (ዘጸ. 19᎑1-6, ዘዳ. 7:6-11) ፣ አብርሐም የጸደቀው ሕገ ኦሪትን በመጠበቁ አልነበረም፣ የእግዚአብሔርን ተስፋ ቃል በማመኑ ነው እንጂ (ዘፍ. 15፡6)። 

2ኛ. የሙሴ ሕግ ሰውን ለማጽደቅ አልተሰጠም። ሕጉ የተሰጠው ከፈርዖን ባርነት ነጻ ለወጣ፣ በበጉ ደም ለተዋጀና ለእግዚአብሔር ለሆነ ሕዝብ (ለዳነ ሕዝብ) መተዳደሪያ እንዲሆን (ዘጸ. 19፡1-25) ተሰጠ እንጂ፣ ከባርነት ነጻ ለመውጣትና ከነዐንን እንዲወርሱ በቅድመ ሁኔታነት አልተሰጠም (ዘዳ. 7፡6-8)።  

3ኛ. ሕጉ ቅዱስ ነው፣ መንፈሳዊም ነው (ሮሜ 7፡ 12-14)፣ ሕጉ የተሰጣቸው ሰዎች (እስራኤላውያን) ሥጋውያን ስለሆኑ ሕጉን መፈጸም ስለማይችሉ እርግማንን ያመጣል (ገላ. 3፡10-11)፤ 

4ኛ. የሕጉ ፍጻሜ ክርስቶስ ስለሆነ ክርስቶስ እስኪመጣ ድረስ በሞግዚትነት እንዲያገለግል በሙሴ በኩል በጊዜያዊነት የተሰጠ ነው (ገላ. 3፡23-25)፣ 

5ኛ. ሕጉ (ኦሪት) የሰዎችን ኃጢአተኛነት፣ የእግዚአብሔርን ቅዱስነት ይገልጣል (ሮሜ 3፡20፣ 7፡7፤ ገላ. 3፡21᎑22)፣ እንጂ ሰዎችን ፍጹማን (ንጹሐን) ማድረግ አይችልም፣ (ገላ. 2፡16፤ ገላ. 3፡11)፤ 

6ኛ. ሕጉ በመሥዋዕቱ፣ በክህነቱ፣ በመቅደሱና በሥርዐቱ፣ ወዘተ. የጥላ አገልግሎት በመሆን የኢየሱስን ቤዛነት በእምነት ለማየት እንዲችሉ ለእስራኤል የተሰጠ ስለሆነ፣ አማናዊው መሥዋዕት፣ መቅደስና ሊቀ ካህናት የሆነው ክርስቶስ ሲመጣ ይሟላል ማለት ነው፣ (ዕብ. 10፡1᎑2)። 

7ኛ. በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት ከጨለማ ሥልጣን እጅ ነጻ ለወጣ የሐዲስ ኪዳን ሕዝብ (ለቤተ ክርስቲያን) መተዳደሪያ እንዲሆን የብሉይ ኪዳኑ ሕግ (ኦሪት) አልተሰጠም፣ ሊሆንም አይችልም። የሐዲስ ኪዳን ሕዝብ በእጅ ሳይሆን በመንፈስ፣ በሥጋው ሳይሆን በልቡ  የተገረዘ ሕዝብ ነው (ሮሜ 2፡29፤ ቆላ. 2: 11) ። ሕጉ በድንጋይ ጽላት ሳይሆን በልብ ጽላት የተጻፈ (2 ቆሮ. 3-3)፣ መሥዋዕቱ የእንስሳት ሳይሆን የክርስቶስ ሥጋና ደም የሆነለት አዲስ ሕዝብ ነው። አምልኮው ምድራዊ ሳይሆን፣ ሰማያዊ፣ ውጫዊ ሳይሆን፣ ውስጣዊ፣ ሥጋዊ ሳይሆን መንፈሳዊ፡ ከሕግ በታች ሳይሆን ከፀጋ በታች (ዮሐ 1:16-17፤ ሮሜ 6:14) የሆነ ሕዝብ ነው። 

አሁን በሐዲስ ኪዳን የኦሪትን ሕግ እንፈጽማለን፣ እናስፈጽማለንም እያሉ ማስተማር በክርስቶስ የተፈጸመውን ሥራ ያለመረዳት፣ ከብርሃን ይልቅ ጨለማን መምረጥ (ዕብ. 6፡4-6)፤ ከነጻነት ወደ ባርነት መምጣት ነው (ገላ. 4፡30-31)።  

በማቴዎስ 5፡17 ላይ የተጠቀሰው በአማርኛ “እኔ ሕግንና ነቢያትን ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ፣ ልፈጽም እንጂ ለመሻር አልመጣሁም፣” የሚለውን ኃይለ ቃል ለመረዳት  “ለመሻር” እና “ልፈጽም” የሚሉትን ሁለት ቃላት (ግሶች) በሚገባ መረዳት ያስፈልጋል። በግእዝ “ኢይምሰልክሙ ዘመጻእኩ እስዐር ኦሪተ ወነቢያተ። ኢመጻእኩ እስዐሮሙ አላ እፈጽሞሙ።” በሚል ይነበባል። “ለመሻር” ና “ልፈጸም” የሚባሉት ሁለት ግሶች ከግእዙ “እሰዐር” እና “እፈጽሞሙ” ከሚለው ፍች ጋር ተስማሚ ናቸው። 

እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስ (አዲስ ኪዳን) በተጻፈበት እናት ቋንቋ በግሪክኛው “ለመሻር” የሚለው ቃል (ግስ) kataluso “ካታሉሶ” (katalusai) to abolish, to destroy፣ “ማጥፋት” “መደምሰስ” ማለት ሲሆን፤ እንዲሁም “ልፈጽም” የሚለው ቃል (ግስ)  በግሪክኛው plero “ፕሌሮ” (plerusai) to fulfill፣ ከሚል ቃል የተገኘ ነው። plero “ፕሌሮ” የሚለው ቃል ትርጉምም  “ማሟላት” “ሙሉ ማድረግ” ማለት ነው። 

በዚህ መሠረት የማቴዎስ 5፡17 ን ንባብ ስንተረጉመው “እኔ ሕግንና  ነቢያትን “ላጠፋ” (“ልደመስስ”) የመጣሁ አይምሰላችሁ፣ “ላሟላ” (“ሙሉ ላደርግ”) እንጂ “ልደመስስ” (“ላጠፋ”) አልመጣሁም። የሚል ይሆናል። ስለሆነም፦

አንደኛ፣ ጌታችን ሕግን “ላሟላ” እንጂ “ልደመስስ”፣ (ላጠፋ) አልመጣሁም በማለቱ፤ ሕጉ እንዲሁ በከንቱ እንዳልተሰጠ፣ እንደማይደመሰስ ነገር ግን “እንደሚሟላ”  ያመለክታል። በዚህም ሕጉ ቅዱስ ቢሆንም ኃጢአተኛውን ሰው መቀደስ፣ ማጽደቅና ፍጹም ማድረግ ባለመቻሉ በክርስቶስ መሟላት የሚያስፈልገው መሆኑን ያሳያል (ዕብ. 7፡18᎐19፤ )።

ሁለተኛ፣ “እኔ ሕግንና  ነቢያትን “ላጠፋ” (“ልደመስስ”) የመጣሁ አይምሰላችሁ፣ “ላሟላ” (“ሙሉ ላደርግ”) እንጂ “ልደመስስ” (“ላጠፋ”) አልመጣሁም፣ በሚለው ኃይለ ቃል ውስጥ “ላጠፋ” እና “ላሟላ” የተባሉት ግሶች የተነገሩት፤ በአንደኛ መደብ ነጠላ ቁጥር ዐቢይ አንቀጽነት ሲሆን፣ “እኔ” በሚል ተውላጠ ስም የተጎላበቱ በመሆናቸው የድርጊቶቹ ፈጻሚ ራሱ ጌታ ኢየሱስ መሆኑን ያሳያል። በዚህም ሕጉን “የማያጠፋውና የማይደመስሰው” ነገር ግን “የሚያሟላው” ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን ያመለክታል። ስለዚህ እኛ እንድናሟላው የተሰጠን ትእዛዝ ያለመኖሩን ያሳያል። 

ሦስተኛ፣ ሕጉ (የብሉይ ኪዳኑ ሕግ) የሚያመለክተውና የሚናገርለት መሢሁ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለመጣ የሕጉ አገልግሎት ፍጻሜ አግኝቷል (ተሟልቷል) ማለት ነው። ስለዚህ ሕጉ ጌታ ኢየሱስ እስኪመጣ ድረስ የሚያገለግል ሞግዚት (ማቆያ) ከሆነና፣ ሕጉ የሚናገርለት ኢየሱስ ከመጣ፤ አሁን በአዲስ ኪዳን የሕጉ አገልግሎት ፍጻሜ ስላገኘ አይቀጥልም ማለት ነው። 

አራተኛ፣ ሰው ከኃጢአቱ የሚነጻው፣ የሚጸድቀውና የእግዚአብሔር ልጅ የሚሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ በሠራው የማዳን ሥራ በማመኑ እንጂ ሕግን በመፈጸሙ አይደለም (ሮሜ 3፡24-28፤ ዮሐ. 1፡12᎐13)። ጳውሎስ እንዳስተማረው “ሰው ያለ ሕግ ሥራ፣ በእምነት እንዲጸድቅ እንቆጥራለን” (ሮሜ 3፡28)፤ “በሙሴም ሕግ ትጸድቁበት ዘንድ ከማይቻላችሁ ሁሉ፣ ያመነ ሁሉ በእርሱ እንዲጸድቅ በእናንተ ዘንድ የታወቀ ይሁን (ሐዋ. 13፡39)ብሎአል። 

5ኛ. በሐዲስ ኪዳን ምእመናን ከሕግ በታች ሁነው ሕግን የሚፈጽሙት ሳይሆን፣ ከጸጋ በታች ሆነው ሕጉ የሚጠይቀውን ብቻ ሳይሆን በአዲስ ሕይወት፣ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል  አብልጠው የሚፈጽሙት የፍቅር ሕግ ነው (ማቴ. 5፡22፤ 28፤ 34፣ 39፤ 44)። 

የሙሴ ሕግ የማያድንና ጊዜያዊ መሆኑን፡የዳንነውና የምንኖረውም በወንጌል ሕግ በፀጋ እንደሆነ፦የኑሲስ ኤጲስ ቆጶስ ጎርጎርዮስ “የፍቅርን ሕግ ወንጌልን ሠራልን ፡ የላም ሥጋ፡ የፍየል ደም ሳንሻ ኃጢአታችንን ማስተስረይ ተቻለን፡ ያች ቀዋሚት ያልነበረች ሕግ ነበረች፡ ድኅነት የማይገኝባት ትእዛዝም ነበረች“ በማለት አስተምሮአል (ሃይማኖተ አበው ዘጎርጎርዮስ)።

ውድ አንባቢ ሆይ! ሕጉ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ከተሟላ በኋላ በብሉይ ኪዳኑ ሕግ ለመኖር መሞከር ሕጉ በኢየሱስ ክርስቶስ እንዳልተሟላ መቁጠር ከመሆኑም በላይ፣ የጌታ ኢየሱስን የማዳን ሥራ፣ ሰው መሆኑን፣ መከራ መስቀሉን፣  መሞትና መነሣቱን እንደ መካድ ይቆጠራል። ለዚህ ነው ሐዋርያው ጳውሎስ  “በሕግ ልትጸድቁ የምትፈልጉ ከክርስቶስ ተለይታችሁ ከጸጋው ወድቃችኋል” (ገላ. 5፡4) ያለው።

ከመምህር ጌታቸው ተረፈ ፌስቡክ የተወሰደ