ነገር ግን እግዚአብሔር በምሕረቱ ባለ ጠጋ ስለ ሆነ፥ ከወደደን ከትልቅ ፍቅሩ የተነሣ በበደላችን ሙታን እንኳ በሆንን ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ሕይወት ሰጠን፥ በጸጋ ድናችኋልና፥ ኤፌ 2፥4-5
Sunday, 20 January 2019
የጌታ ክብር መገለጥ (ክፍል አራት)
" ኢየሱስም። አንቺ ሴት፥ ከአንቺ ጋር ምን አለኝ? ጊዜዬ ገና አልደረሰም አላት። " (ዮሐ 2፥4)
በዚህ ቁጥር ላይ ሦስት መሰረታዊ ጥያቄዎችን በመመለስ እንዳስሳለን። እነዚህ ጥያቄዎች ለብዙ ዘመናት ሲያከራክር የቆዩና አሁንም ድረስ ብዙዎችን ያላግባቡ ጉዳዮች ናቸው።
1) አንቺ ሴት ለምን አላት?
2) ካንቺ ጋር ምን አለኝ ሲል ምን ለማለት ነው?
3) ጊዜዬ ገና አልደረሰም ምንድነው?
አንቺ ሴት:-
'' አንቺ ሴት '' የሚለውን አንዳንዶች ጌታ እናቱን ለመቃወም አድርገው ይወስዱታል ሌሎች ደግሞ የተለየ ክብር ለመስጠት የተደረገ ንግግር ነው ብለው ያምናሉ። በእኛ ባህል አንዲትን ሴት ስም እያላት አንቺ ሴት ማለት ነውር (ክብርን የሚነካ) ሊሆን ይችላል በሌለ አካባቢ ደግሞ ክብርን ሊያሳይ ይችላል። ለአብነት ያህል ነጭ ልብስ በእኛ ሀገር የደስታ ማሳያ ሲሆን በህንድ ግን የሀዘን ነው ስለሆነም ስለ ህንድ በእኛ ባህል ጆሮ መስማት የለብንም። አንቺ ሴትን ከተቻለ በእስራኤል ካልሆነ በመፅሐፍ ቅዱስ ዘይቤ መስማት አለብን። ታዲያ ጌታ እናቱ መሆኗን እያወቀ ለምን አንቺ ሴትን መረጠ? ጌታ ይህን ቃል የተጠቀመው ለመንቀፍ (ለመቃወም) ወይም የተለየ ክብር ለመስጠት መሆኑን በመፅሐፍ ቅዱስ ማስታረቅ ይኖርብናል።
ጌታ ኢየሱስ '' አንቺ ሴት '' የሚለውን አጠራር በሌላ ስፍራ ተጠቅሞታል። '' አንቺ ሴት እመኚኝ '' (ዮሐ 4፥21) እንዳለ ለሳምራዊቷ ሴት ለመንቀፍ ወይም የተለየ ክብርን ለመስጠት እንዳልጠቀመበት ማየት እንችላለን። ስለሆነም ማንኛውም የአይሁድ ወንድ ሴቶችን የሚጠራበት በባህላቸው ተቀባይነት ያለው መደበኛ አጠራር ወይም ንግግር ነው። ጌታም የተለየ ክብር መስጠት ቢፈልግ እናቴ ይላት ነበር። የድንግል ማርያም ልዩ ክብር ጌታን መውለዷ ነውና። በሌላ በኩል ማቅለል ወይም ማዋረድም እንዳይደለ በሌላ ስፍራ ጌታ ይህንኑ ቃል ለእናቱ የተጠቀመበትን ሁኔታ ማየት ይኖርብናል።
" ኢየሱስም እናቱን ይወደው የነበረውንም ደቀ መዝሙር በአጠገቡ ቆሞ ባየ ጊዜ እናቱን። አንቺ ሴት፥ እነሆ ልጅሽ አላት። " (ዮሐ 19፥26) እዚህ ጋር ጌታ ለእናቱ ያለውን መራራት ያሳያል ስለሆነም ይህ አጠራር ነቀፌታ እንደሌለው ማየት ይቻላል።
ከአንቺ ጋር ምን አለኝ:-
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክ የአንድምታው ትርጓሜ ለዚህ ክፍል በሊቃውንቶቿ የተሰጡት አንድምታዊ ትርጓሜዎች እንዲህ የሚሉ ናቸው።
ሀ) " አንድም ካንች ጋር ምን አለኝ? ማለት ውሃውን ወይን ጠጅ አድርግላቸው ብትይኝ አይሆንም እልሽ ዘንድ ካንች ጋር ምን ፀብ አለኝ? "
ይህ አተረጓጎም ሙሉ በሙሉ አዎንታዊ ነው። ኢየሱስ የእናቱን ጥያቄም ሆነ ምክንያቷን ተቀብሎ አድርጎላታል የሚል ፍቺ ያለው አተረጓጎም ነው።
ለ) " አንድም ውሃውን ጠጅ አድርግላቸው ብትዪኝ አይኾንም እልሽ ዘንድ ውሃውን ጠጅ ላላደርግላቸው ከሰርግ ቤት ተጠርቼ መጥቻለሁን? ውሃውን ጠጅ ላላደርግላቸው ነውን? አላት። "
ይህ ደግሞ የእናቱን ጥያቄ ተቀብሎም አይደለም ተገዶም አይደለም ውሃውን የወይን ጠጅ የሚያደርገው የሚል ፍቺ አለው ወይም ተአምር የሚያደርገው በእሷ ሀሳብ ላይ ተመስርቶ አይደለም የሚል አንድምታ አለው። ወደ ሰርግ ቤት የመጣሁት ይህን ላደርግ ነው እንጂ ላላደርግ አይደለም ነው።
ሐ) " አንድም ውሃውን ወይን ጠጅ አድርጌ የማጠጣቸው በኔ ፈቃድ ነው እንጂ ባንቺ ትዕዛዝ ነውን አላት "
ይህ ደግሞ ከሌሎቹ አተረጓጎም ይለያል። ጌታ ይህን ያለው በመቃወም እንደሆነና በአምላክነቱ አገብሮ (መገደድ/መታዘዝ) እንደሌለበት ለማጠየቅም (ለማረጋገጥ) እንደሆነ ነው። በማንም ትዕዛዝ የማይሰራ እንደሆነ ለማሳየት ጭምርና ውሃውን ወደ ወይን ጠጅ የማደርገው በራሴ ፈቃድ ላይ ተመስርቼ ነው የማደርገው ለማለት ነው '' ካንቺ ጋር ምን አለኝ '' ያለው ተብሎ ተተርጉሟል።
ከነዚህ አማርኛ አንድምታዊ ትርጓሜ በፊት የነበረው የግዕዝ በግዕዝ ትርጓሜ ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለድንግል ማርያም ጥያቄ የመለሰውን መልስ በተመለከተ '' አንቺ ሴት፥ ከአንቺ ጋር ምን አለኝ? ጊዜዬ ገና አልደረሰም '' የሚሉትን ሶስት ሀሳቦች ጠቅልሎ በመያዝ የሚከተለውን ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡
" ወዘይቤሂ ኢበጽሐ ጊዜየ ዘንተ ይቤ እም ፍናወ ተግሣጽ ለእሙ ወፍካሁሰ ምንተ ትገብሪ እንበይነ ተጊሆትየ ለገቢረ ዝንቱ ተአምር፡፡ አኮ ከመ ሙሴ ወእለ ቀደሙኒ በዘመን እሙር (ዘከመ ትሩፍ ላዕሌሁ) ወባሕቱ እስመ ክሂሎትየ ላዕለ ዝንቱ ግብር ዘልፈ ውእቱ ። ጊዜ ፈቀድኩ እገበር፡፡ ወባሕቱ ኢትትላኰዪ ከመ በዝንቱ ቃል ታልዕልኒ ሶበ ሰአልክኒ ሊተ፡፡ወእመኒ ኢሰአልክኒ ሀለወኒ እግበር ወአርኢ አምላክናየ፡፡ ወበእንተዝ ጸንአት ወትቤሎሙ ለላእካን ርእዩ ዘይቤ ወግበሩ፡፡ ወይእቲሰ ለበወት እምቃሉ በአይ ጊዜ ፈቀደ ገቢረ ይገብር፡፡ ይደሉ እንከ ይኩን ቃሉ ተግሣጸ ላቲ፤ ወብሂለ ኢበጽሐ ጊዜየ እትጌበር በርእስየ ወአልብኪ ግብር ላዕሌየ፡፡ "
ትርጉም
" ጊዜዬ ገና አልደረሰም በማለቱ ለእናቱ በተግሣጽ መንገድ ተናገራት፤ ትርጕሙም ይህን ተአምር ለማድረግ እተጋ ዘንድ ምን ማድረግ ትችያለሽ? እኔ በወደድሁ ጊዜ አደርገዋለሁ ማለት ነው፡፡ ከእኔ በዘመን ቀድመው (ከእኔ በፊት) እንደነበሩ እንደ ሙሴና እንደሌሎች ነቢያት አይደለሁም፤ ነገር ግን ይህን ተአምር የማድረግ ችሎታዬ ሁልጊዜም ከእኔ ጋር ነውና በወደድሁ ጊዜ አደርገዋለሁ፤ ነገር ግን አንቺ በለመንሽ ጊዜ በዚህ በልመና ቃልሽ ታነሳሽኝ ዘንድ አትዘብዝቢኝ፤ (ደጋግመሽ አትጠይቂኝ) ባትለምኚኝም ተአምር አድርጌ አምላክነቴን እገልጥ ዘንድ አለኝ አላት፡፡ ስለዚህ እርሷ በርትታ ለአገልጋዮች የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ አለቻቸው፡፡ እርሷ ግን በወደደው በየትኛውም ጊዜ ሊያደርገው እንደሚችል አስተዋለች፤ እንኪያስ ቃሉ ለእርሷ ተግሣጽ እንደነበረ ልንረዳው ይገባል፡፡ ጊዜየ ገና አልደረሰም ማለቱም እኔ በወደድሁ ጊዜ አደርገዋለሁ፤ አንቺ ልታዝዢኝ አትችይም ማለቱ ነው፡፡ ''
እነዚህ አንድምታዊ ትርጕሞች በሙሉ አንድም የምልጃን ሐሳብ አይገልፁም። ድንግል ማርያም በእናትነትዋ ላቀረበችው ጥያቄ ጌታ የሰጣትን ምላሽ በአንድምታው መሠረት ሊቃውንቱ የሰጡት ትርጕም ምልጃዊ መልክ አላቸው ብለን ልንወስደው አያስችለንም። ይልቁንም የጌታ ምላሽ ውስጥ እርሱ ታዝዞ የሚያደርገው ነገር እንደሌለና እንደ ራሱ ሀሳብና ፈቃድ ተመስርቶ ብቻ እንደሚያደርግ የሚያሳይ ነው።
መልእክቷን ወይም ጥያቄዋን ተቀብሏል ወይስ ተቃውሞታል ለሚለው ተቀብሎታል ነገር ግን ጥያቄውን ይዛ የመጣችበትን መንገድ (Intention) ግን ተቃውሞታል። የእሷን ጥያቄ በራሱ መለኮታዊ አጀንዳ (ፕሮግራም) ውስጥ አስገባው። የእሱ ድርጊት የእሷን ጥያቄ መለሰ እንጂ የእሷ ጥያቄ እሱን ለማድረግ አላነሳሳውም (cause አላደረገውም)።
ጊዜዬ ገና አልደረሰም:-
ጊዜዬ ገና አልደረሰም ለሚለው የአንድምታ ትርጓሜ
1) ገና የወይን ጠጁ ተንጠፋጥፎ አላለቀም ለማለት እንደሆነ ጭምር ይናገራል ነገር ግን ድንግል ማርያም በቦታው አረጋግጣ ያለችው ስለሆነ ለመቀበል ይከብዳል።
2) ይሁዳ ወቶ ነበርና እስኪመለስ ድረስ እየተጠበቀ ነው የሚል ትርጉም ተሰጥቶታል። ምክንያቱም ከተአምራቱ ቢያስወጣኝ በሞቱ ገባሁበት ይላልና ተአምሩን እንዲያይ የሚል አንድምታዊ ትርጉም ተሰጥቶታል። ነገር ግን እዚህ ጋር ይሁዳ ይኑር አይኑር የሚታወቅ ነገር የለም። ይህን ፍራቻ የሚያስቀር ጌታ ይሁዳ ባለበት በተደጋጋሚ ተአምር አድርጓልና። እዚህ ጋር ይኑር አይኑርም በሌላ ስፍራ ያየው ተአምር ወይም ወንጌል ይገዛዋልና።
ጊዜዬ ገና አልደረሰም የሚለው ቃል በዚሁ በዮሐንስ ወንጌል በተደጋጋሚ ተጠቅሶ እናገኘዋለን። ለአብነት ያህልም
"፤ ኢየሱስም እንዲህ አላቸው። ጊዜዬ ገና አልደረሰም፥ ጊዜያችሁ ግን ዘወትር የተመቸ ነው። " (ዮሐ 7፥6)
"፤ ስለዚህ ሊይዙት ይፈልጉ ነበር፤ ነገር ግን ጊዜው ገና ስላልደረሰ ማንም እጁን አልጫነበትም። " (ዮሐ 7፥30)
"፤ ኢየሱስ በመቅደስ ሲያስተምር በግምጃ ቤት አጠገብ ይህን ነገር ተናገረ፤ ጊዜው ገና አልደረሰምና ማንም አልያዘውም። " (ዮሐ 8፥20)
እነዚህ በሙሉ የሚያሳዩት ጌታ ለመጣበት ዓላማ የሚያደርገውን የቤዛነት ጉዞ የሚያስረዱ ናቸው። ይህ '' ጊዜ '' የሚለው ሲደርስ ወደ ሰአት ሲቀየርም መጽሐፍ ቅዱሳችን ይናገራል።
" አሁን ነፍሴ ታውካለች ምንስ እላለሁ? አባት ሆይ፥ ከዚህ ሰዓት አድነኝ። ነገር ግን ስለዚህ ወደዚህ ሰዓት መጣሁ። " (ዮሐ 12፥27) ለዚህም ነው ቀጣዩ ምዕራፍ ሲጀምር ጌታ ከዚህ ዓለም ወደ አብ የሚሄድበት ሰዓት እንደ ደረሰ አውቆ፥ የሚለው። (ዮሐ 13፥1) ስለሆነም ጊዜዬ ገና አልደረሰም የሚለው የጌታ ምላሽ አሁንም ምላሽ እየሰጠው ነው ገና ወደ ሞት አልደረስኩም የሚል ፍቺ አለው። የማደርገው ምልክት ሞቴን ይናገራል እንጂ አሁን ጊዜዬ ገና አልደረሰም እያለ ነው።
ጌታ ኢየሱስ ከወይን ጠጅ ጉዳይ በቀጥታ ወደ ሞቱ ወሰደው። ሰርግ ቤት ሆኖ የቀራኒዬን ሞት ማሳየት ጀመረ።
" እናቱም ለአገልጋዮቹ። የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ አለቻቸው። " (ዮሐ 2፥5)
ይህ የድንግል ማርያም የእምነት ቃል ነው። ልጇ አንድ ተአምር እንደሚያደርግ ተማምናለች። የመጣችበት መንገድ ምንም ይሁን ብቻ የመጣችበት ጉዳይ ግን ሊፈፀም እንደሚችል አውቃለች። ለዚህም ነው የሚላችሁን አድርጉ ያለችው።
" አይሁድም እንደሚያደርጉት የማንጻት ልማድ ስድስት የድንጋይ ጋኖች በዚያ ተቀምጠው ነበር፥ እያንዳንዳቸውም ሁለት ወይም ሦስት እንስራ ይይዙ ነበር። " (ዮሐ 2፥6)
እዚህ ጋር ታሪኩ ሙሉ በሙሉ ከሰርግ ወደ ሃይማኖት ሲቀየር እናነባለን። ጊዜዬ ገና አልደረሰም ስንል ሞቱን እንደሆነ አይተናል ስለሆነም ይህ ሞት ደግሞ የሚለጠው ወይም የሚፈፀመው በሰርግ ሳይሆን በሃይማኖት አጀንዳ ስር ነው። ጌታም ለሰርጉ የወይን ጠጅ ማዘጋጃ ጋንን ትቶ በቀጥታ ወደ ሃይማኖት ስርአት ወደሚፈፀምባቸው ጋኖች ነው የሄደው። ጉዳዩን ከማህበራዊ አጀንዳ ወደ ሃይማኖት (መንፈሳዊ) ቀየረው። እነዚህ የመንፃት ጋኖችና ውሃ የኢየሱስ የመስሪያ ቦታ መሆኑንም እየጠቆመ ነው። ጌታ በቤተክርስቲያን ላይ በሆነው ሙሽራነቱ እንዴት ሙሽሪቱን እንደሚያነፃ እያሳየ ነው። በሞቱና በደሙ የሰውን ኃጢአት እንዴት እንደሚያነፃ እያሳየ ነበር ነገር ግን ማንም አላስተዋለም።
ይቀጥላል................
Subscribe to:
Posts (Atom)